Exodus 34

አዲሶቹ የድንጋይ ጽላቶች

1 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን አለው፤ “እንደ መጀመሪያዎቹ ያሉ ሁለት የድንጋይ ጽላቶች ጥረብ፤ እኔም አንተ በሰበርካቸው በመጀመሪያዎቹ ጽላቶች ላይ የነበሩትን ቃሎች እጽፍባቸዋለሁ። 2በማለዳ ተዘጋጅተህ ወደ ሲና ተራራ ውጣ፤ በዚያ በተራራው ጫፍ ላይ በፊቴ ቁም፤ 3ከአንተ ጋር ማንም እንዳይመጣ ወይም በተራራው ላይ በየትኛውም ቦታ እንዳይታይ፤ የበግና የፍየል መንጋዎች የቀንድ ከብቶችም እንኳ፣ በተራራው ፊት ለፊት መጋጥ የለባቸውም።”

4ስለዚህ ሙሴ እንደ መጀመሪያዎቹ ያሉ ሁለት የድንጋይ ጽላቶች ጠርቦ፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዳዘዘው በማለዳ ወደ ሲና ተራራ ወጣ፤ ሁለቱን የድንጋይ ጽላቶችም በእጆቹ ያዘ። 5ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) በደመና ወረደ፤ በዚያም ከእርሱ ጋር ቆሞ ስሙን እግዚአብሔርን (ያህዌ) ዐወጀ። 6እርሱም በሙሴ ፊት እንዲህ እያለ እያወጀ ዐለፈ፤ “እግዚአብሔር (ያህዌ) ርኅሩኅ ቸር አምላክ፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) ለቍጣ የዘገየ፣ ፍቅሩና ታማኝነቱ የበዛ፣ 7ፍቅርን ለሺዎች የሚጠብቅ፣ ክፋትን፣ ዐመፅንና ኀጢአትን ይቅር የሚል፣ በደለኛውን ግን ሳይቀጣ ዝም ብሎ አይተውም፤ በአባቶች ኀጢአት ልጆችን የልጅ ልጆቻቸውን እስከ ሦስትና አራት ትውልድ ይቀጣል።”

8ሙሴም ወዲያውኑ ወደ መሬት ዝቅ ብሎ ሰገደ፤ 9“አቤቱ ጌታ (አዶናይ) ሆይ፤ በፊትህ ሞገስ አግኝቼ ከሆነ፣ ጌታ (አዶናይ) ከእኛ ጋር ይሂድ፤ ይህ ዐንገተ ደንዳና ሕዝብ ቢሆንም እንኳ፣ ክፋታችንንና ኀጢአታችንን ይቅር በል፤ እንደ ርስትህም አድርገህ ውሰደን።”

10ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዲህ አለ፤ “ከአንተ ጋር ኪዳን እገባለሁ፤ ከዚህ ቀደም በዓለም ሁሉ ለየትኛውም ሕዝብ ከቶ ያልተደረገ፣ በሕዝብህ ሁሉ ፊት ድንቅ አደርጋለሁ፤ በመካከላቸው አብረሃቸው የምትኖር ሕዝብ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ለአንተ የማደርግልህ ሥራ የቱን ያህል አስፈሪ እንደ ሆነ ያያሉ። 11ዛሬ የማዝህን ፈጽም፤ አሞራውያንን፣ ከነዓናውያንን፣ ኬጢያውያንን፣ ፌርዛውያንን፣ ኤዊያውያንንና ኢያቡሳውያንን በፊትህ አስወጣቸዋለሁ። 12ከምትሄድበት አገር ነዋሪዎች ጋር ቃል ኪዳን እንዳታደርግ ተጠንቀቅ፤ አለዚያ በመካከልህ ወጥመድ ይሆኑብሃል። 13መሠዊያዎቻቸውን ሰባብሩ፤ የማምለኪያ ዐምዶቻቸውን አድቅቁ
አሼራ የምትባለውን ጣዖት አምላክ ምስል ማለት ነው።
፤ የአሼራ ዐፀዶቻቸውንም ቍረጡ።
14ስሙ ቀናተኛ የሆነው እግዚአብሔር (ያህዌ) ቀናተኛ አምላክ (ኤሎሂም) ነውና ሌላ አምላክ አታምልክ።

15“በምድሪቱ ከሚኖሩት ጋር ቃል ኪዳን እንዳታደርግ ተጠንቀቅ፤ ምክንያቱም አምላኮቻቸውን ተከትለው ባመነዘሩና መሥዋዕትም ባቀረቡላቸው ጊዜ ይጋብዙሃል፤ አንተም መሥዋዕታቸውን ትበላለህ። 16ለወንዶች ልጆችህም ሴቶች ልጆቻቸውን ስታጭላቸውና እነዚህም ሴቶች ልጆች አምላኮቻቸውን በመከተል ሲያመነዝሩ፣ ወንዶች ልጆችህን ተመሳሳይ ድርጊት እንዲፈጽሙ ያነሣሷቸዋል።

17“ቀልጠው የሚሠሩ አማልክትን አታብጅ።

18“የቂጣን በዓል አክብር። እንዳዘዝሁህም ለሰባት ቀን እርሾ ያልገባበት ቂጣ ብላ፤ ይህንም በተወሰነው ጊዜ በአቢብ ወር አድርግ፤ በዚያ ወር ከግብፅ ወጥተሃልና።

19“የመንጋህ ወይም የበግና የፍየልህ፣ የቀንድ ከብትህ ተባዕት በኵር ሁሉ ሳይቀር፣ ከማሕፀን በኵር ሆኖ የሚወጣ ሁሉ የእኔ ነው። 20የአህያን በኵር በበግ ጠቦት ዋጀው፤ ካልዋጀኸው ግን ዐንገቱን ስበረው። በኵር ወንድ ልጆችህን ሁሉ ዋጅ።

“ማንም በፊቴ ባዶ እጁን አይቅረብ።

21“ስድስት ቀን ሥራ፤ በሰባተኛው ቀን ግን ዕረፍ፤ በዕርሻና በመከር ወቅት እንኳ ቢሆን ማረፍ አለብህ።

22“የሰባቱን ሱባዔ በዓል ከስንዴው መከር በኵራቶች ጋር፣ እንዲሁም የመክተቻ በዓልን በዓመቱ መጨረሻ
በዚያ አካባቢ ክረምት መግቢያ ላይ ማለት ነው።
ላይ አክብር።
23በዓመት ሦስት ጊዜ ወንድ ሁሉ በእስራኤል አምላክ (ኤሎሂም) በጌታ እግዚአብሔር (አዶናይ ያህዌ) ፊት ይቅረብ። 24አሕዛብን ከፊትህ አስወጣለሁ፤ ድንበርህን አሰፋለሁ፤ በዓመት ሦስት ጊዜ በአምላክህ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ለመቅረብ ስትወጣ፣ ምድርህን ማንም አይመኝም።

25“እርሾ ካለው ከማንኛውም ነገር ጋር የደም መሥዋዕት ለእኔ አታቅርብ፤ ከፋሲካ በዓል የተረፈው መሥዋዕት እስከ ማለዳ አይቈይ።

26“የዐፈርህን ምርጥ በኵራት ለአምላክህ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ቤት አምጣ።

“ጠቦት ፍየልን በእናቱ ወተት አትቀቅል።”

27ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን፣ “እነዚህን ቃሎች ጻፋቸው፤ በእነዚህ ቃሎች መሠረት ከአንተና ከእስራኤል ጋር ቃል ኪዳን አድርጌአለሁና” አለው። 28ሙሴ እህል ሳይበላ፣ ውሃም ሳይጠጣ ከእግዚአብሔር (ያህዌ) ጋር አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በዚያ ነበር፤ በጽላቶቹ ላይ የቃል ኪዳኑን ቃሎች፣ ዐሥርቱ ትእዛዛትን ጻፈ።

የሚያበራው የሙሴ ፊት

29ሙሴ ሁለቱን የምስክር ጽላቶች በእጆቹ ይዞ ከሲና ተራራ በወረደ ጊዜ ከእግዚአብሔር (ያህዌ) ጋር ከመነጋገሩ የተነሣ ፊቱ እንደሚያበራ አላወቀም ነበር። 30አሮንና እስራኤላውያን ሁሉ ሙሴን ባዩት ጊዜ ፊቱ ያበራ ነበር፤ ወደ እርሱ ለመቅረብም ፈርተው ነበር። 31ሙሴ ግን ጠራቸው፤ ስለዚህ አሮንና የማኅበሩ መሪዎች ወደ እርሱ ተመለሱ፤ እርሱም አናገራቸው። 32ከዚያም በኋላ እስራኤላውያን ሁሉ ወደ እርሱ ቀረቡ፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) በሲና ተራራ የሰጠውን ትእዛዞች ሁሉ ሰጣቸው። 33ሙሴ ለእነርሱ ተናግሮ ከጨረሰ በኋላ በፊቱ ላይ መሸፈኛ አደረገ። 34ከእርሱ ጋር ለመነጋገር ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ሀልዎት በሚገባበት ጊዜ ሁሉ ግን፣ እስከሚወጣ ድረስ መሸፈኛውን ያነሣ ነበር፤ በወጣም ጊዜ የታዘዘውን ለእስራኤላውያን ነገራቸው። 35ፊቱ የሚያበራ መሆኑን አዩ፤ ከዚያም ሙሴ ከእግዚአብሔር (ያህዌ) ጋር ለመነጋገር ተመልሶ እስኪሄድ ድረስ መሸፈኛውን መልሶ በፊቱ ላይ ያደርግ ነበር።

Copyright information for AmhNASV